ምን እየተደረገ ነው


ይህ መረጃ በተለይ የፍሊንትስቶን ሆምስ ደንበኞች በፕሮጄክቶቻቸው የሥራ ሂደት ላይ ተገቢው፣ ወቅታዊና ትክክለኛው መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ መረጃውን በመጠቀም ደንበኞች እንደየሥጋታቸው መጠን ተጨማሪ መረጃ መጠየቅም ሆነ በዚህ መረጃ ላይ ተመሥርተው የውል መብታቸውን ለማስከበር ያስችላቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለበት የቤት ልማት የሥራ ሂደት ለአልሚውም ሆነ ለደንበኛው ደህንነት እና ለሁሉም ፕሮጀክቶች ስኬት ወሳኝ ነው፡፡

ከግንቦት ወር መጨረሻ 2010 ዓ.ም የፍሊንትስቶን ሆምስ ፕሮጄክቶች ከኢኮኖሚው አለመረጋጋት የተነሳ በከፍተኛ ሥጋት ላይ ሆነው አጠቃላይ ሁኔታውን በአካል ቀርበን እንድናስረዳ ደንበኞች በጠየቁት መሠረት ካደረግናቸው ተከታታይ ስብሰባዎች በኋላ የተካሄዱት እንቅስቃሴዎች በሙሉ ከሞላ ጎደል በዚያኔው ስብሰባዎች ከተቀመጡ አጠቃላይ አቅጣጫዎች በመነሳት የተፈጸሙ ናቸው፡፡(የስብሰባዎቹን ውጤት እዚህ ይመልከቱ) https://www.flintstonehomes.com/facts-about-flintstone/3


ምን ተደረገ

የአደይ በሻሌ ሳይት የጠቅላላ ቤቶች ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ ነው፡፡ በወቅቱ የተሸጡት ቤቶች ቁጥር ግማሽ ብቻ ሲሆን ከተከፈለው ጋር ተባዝቶ የፕሮጄክቱ ቀሪ ገንዘብ ሲሰላ ሥጋቱን ለመቋቋም ምን ማድረግ እንደሚሻል ከመወሰን በፊት ንቁም በህላዌ  ባለንበት እንቁም የሚያስብል ነበር፡፡ ሆኖም መጭው ጊዜ ክረምት ስለነበር እና የመሠረት ብረት ፍጆታውም ከፍተኛ በመሆኑ በአደይ በሻሌ ሳይት ላይ በጊዜው የመሰረት ስራን አፋጥነን ቀሪውን ስራ ኢኮኖሚዉ እስከሚረጋጋ ዝግ ብለን በመሥራት  አሳልፈናል ፡፡ ይህም ምንም እንኳን ብዙ ደንበኞች ዋጋ ጨምረን የበለጠ ለመክፈል ፈቃደኝነታቸውን ቢያሳዩንም ነበር፤ የበለጡ ደንበኞችም ለመግዛት ቢፈልጉም ሽያጩንም አቁመን ቆይተናል፡፡ ሆኖም ወጭን ሊቀንሱ ይችላሉ ብለን በገመትንባቸው በዲዛይን እና በአገር ውስጥ የግዥ ኮንትራቶች የውጭ ምንዛሪ የግብዓት ቅነሳ ላይ በርካታ ሥራ ሠርተናል :: በመቀጠልም፣ ያለማቋረጥ የምንገነባው ለሙሉ ፕሮጄክቱ መጠን በመሆኑ፣ የምንሸጠው እና የምንሠራው መጠን ስለማይመጣጠን፣ ይህን ለማካካስ የተሰራውን ያህል መጠን ገንዘብ በብድር ወደ ስራ ማስገባት ተገቢ መሆኑን በማመን ብድር ለመበደር ተወስኗል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም በድርጅታችን ያልተሞከረ የፋይናንስ ሞዴል በመሆኑ ለፍሊንተትስቶን ፕሮጄክቶችና ደንበኞች የገበያውን ተግዳሮት ለመቋቋም የሚያስችል አዲስ አቅም ሆኗል፡፡


 ምን እየተደረገ ነው

ባልተረጋጋ የገበያና የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የፕሮጀክቶቹን ስጋት በሁለት ከፍሎ ማሰብ ይገባል የመጀመሪያው የሥጋት ደረጃ የፕሮጄክቱ የተናጥል የይዞታ ማረጋገጫ እስከሚገኝበት እስከ 85 በመቶ ስትራክቸር መጨረስና እና ካርታ ሽንሻኖ ማስጀመር እስከሚቻልበት ያለው ምዕራፍ ማጠናቀቂያ ነው፡፡ ሁለተኛው የማጠናቀቂያ ስራ ተሠርቶ፣ ርክክብ እና መብራትና ውሀን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ከከተማው ማስገባት የሚቻልበት ደረጃ ላይ እስከሚደረስ ያው ነው፡፡ እነዚህን ለሁለት ከፍሎ የመጀመሪያውን የስትራክቸር እና የካርታ ሽንሻኖ ስራ በሰኔ 2013 ለመጨረስ ታቅዷል ፡፡

ብድር መልካም አማራጭ ቢሆንም - ሊገኝ የሚችለው የብድር መጠን ከተሰራው ሥራ የገንዘብ መጠን ያነሰ በመሆኑ የግድ የደንበኞችን ገንዘብ በፍጥነት መሰብሰብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይህ የደንበኞች ገንዘብ ከሥራው ፍጥነት እኩል የሚሰበሰብበት መንገድ ሦስት ጉዳዮችን የያዘ ነው፤ የነባር ደንበኞችን እምነት ማጠናከር፣ በቀድሞ ውል ውስጥ ያለውን የክፍያ ምዕራፍ ወደ ሦስት ተመጣጣኝ የማይልስቶን ክፍልፋዮች በመሸንሸን እና የአዲስ ደንበኞችን ለገበያው መዋዠቅ ሥጋትን መጋራትን ያካትታል፡፡ እነዚህም በዝርዝር የሚከተሉትን ይመስላሉ፤

1.    ያልተከፈሉ ተሰብሳቢዎችን መሰብሰብ

የማይልስቶን ክፍያዎች በሰዓቱ አለመሰብሰባቸው ዋነኛ ምክንያቶች የደንበኞች ስጋት ናቸው

        • የግንባታም ፤ የሽያጭም ፤ የማስታወቂያ ስራም መቆሙ ለክፍያ የሚያበረታታ አለመሆኑ፤

        • የግንባታ ስራው ጥንቅቅ ያለ ባለመሆኑ ደንበኞች የውስጥ አቅማችን ላይ እንዳይተማመኑ ማድረጉ፤

        • በኢኮኖሚው አለመረጋጋት ምክንያት የተፈጠረ የገበያ መረበሽ መፈጠሩ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ምንም ወቅቱ ከኮሮና መምጣት ጋር ተያያዥ የሆኑ ስጋቶች ያሉበት ቢሆንም ከጀመርነው ፈጣን የግንባታ ሂደት እና ተያያዥ የሆኑ የውስጥ አቅም ዝግጅት እንዲሁም በኢኮኖሚው በተወሰነ መልኩ ከመጡት ለውጦች ጋር ተዳምሮ ያልተከፈሉ ተሰብሳቢዎችን ለመሰብሰብ የሚያበቃ የደንበኞችና የአልሚ መተማመን እና መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ በሂደት ይህ መተማማን ከፕሮጄክቶቹ ስራ ጋር አብሮ ይዳብራል ፡፡

2. የማይልስቶን ክፍያን በመሸንሸን ደንበኞችን ለትንሽና ቶሎ ቶሎ (small & frequent) ክፍያ ማዘጋጀት

 ከዚህ በፊት በነበረን አሰራር በአዴ በሻሌ ፕሮጄክት ከመሠረት በኋላ በአንድ ብሎክ ( ባለ 12 ፎቅ ህንጻ) ሦስት ወለሎች ሲገነቡ አንድ የክፍያ ምዕራፍ ይሞላ ነበር፡፡ በርግጥ ደንበኛው በፈቃደኝነት ስራው የማይልስቶን ክፍያ ላይ ሳይደርስም በክፍያ ማበረታቻ ቅናሽ አስቀድሞ ይከፍል ነበር፤ ከዛም አልፎ በየወሩ ደንበኞች የሚከፍሉበት አሰራርም እንደነበረ ይታወቃል (በተለይ ከአዲስ አበባ ርቀው በክልልም ሆነ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ)፡፡ በዚህ ሰዓት ግን ከእነዚህ የአከፋፈል አካሄድዎች በተጨማሪ ከሁሉም ደንበኞች እኩል ገንዘብ በተመሣሣይ ወቅት ቢሰበሰብ የሚፈጥረው አቅም መብለጡ ታምኖበት የማይልስቶን ክፍያ ሽንሻኖ ተዘጋጅትዋል ፡፡ የማይልስቶን ክፍያን መሸንሽን ማለት ክፍያን በኮንስትራክሽን ሂደት / በፕሌን መደርደር / ማስቀመጥ ነው ፡፡ በቀድሞ ውል ውስጥ ያለውን የክፍያ ምዕራፍ ወደ ሦስት ተመጣጣኝ የማይልስቶን ክፍልፋዮች በመሸንሸን በደንበኛ ውል አንቀጽ 3 የተዘረዘረው የአከፋፈል ስርዓትን ጊዜ ሳይነኩ የስራውን ሂደት በመበተን ከፍያውን ከስራው ሂደት ጋር በአጫጭር እርከኖች ተያያዥ ማድረግ ነው ፡፡

ለምሳሌ ከዚህ በፊት ፤

ቀድሞ የነበረው

Planes

ክፍያ %

Months

At completion of foundation

15%

2nd

At completion of 3rd floor plane

10%

5th


 በአዲስ የማይልስቶን ሽንሽኖ የተቀየረው  

Planes

ክፍያ %

End of Month

At completion of foundation

15%

2nd

At completion of 1st floor plane

4%

3rd

At completion of 2nd floor plane

3%

4th

At completion of 3rd floor plane

3%

5th


3. በዋጋ ማስተካከያ /price adjustment /አዳዲስ ሽያጮችን ማካሄድ 

የፍሊንትስቶን ሆምስ የቀድሞ ኮንትራቶች በPrice Adjustment የሚስተናገዱ ነበሩ፡፡ ድርጅቱና ደንበኞች የገበያ ዋጋ ጭማሪን፣ የውጭ ምንዛሪን ለውጥም ጨምሮ በጋራ ተጋርተው ብዙ የተሳኩ ፕጄክቶች አጠናቅቀዋል፡፡ ሆኖም በ2004 መጨረሻ አካባቢ በተፈጠረው የገበያ መረጋጋትና የመንግሥት የጸረ ግሽበት ፖሊሲ መጠናከር የተነሳ፣ ፍሊንትስቶን ሆምስ ዋጋን ከገበያ ጋር የማስተካከል ኃላፊነት የአልሚው እና የመንግሥ እንጂ የደንበኛው ኃላፊነት አይደሉም በማለት ውሎች ወደ ቁርጥ ዋጋ እንዲቀየሩ አድጓል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ድርጅቱ በዋጋ መናር ላይ የመከላከል ሥራ እና የሥርጸትና ምርምር ስራውን እንዲያረታ ቢያደርገውም፣ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ፍጥነት፣ የሀገራዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚው አለመረጋጋትን ጨምሮ በዋጋ ማስተካከያ /price adjustment /አዳዲስ ሽያጮችን ማካሄድን እንደገና እንዲያመዛዝን አስገድዶታል፡፡ አዳዲስ ገዥዎች የሚተናገደበት የቁርጥ ዋጋ አማራጭ እና የዋጋ ማስተካካያ አማራጭም ተዘገጅቷል፡፡

አንደኛ አማራጭ ሁሉም ፕሮጀክቶች ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ሽያጭ የተከናወነበትን ወር ዋጋ የውሉ ዋጋ በማድረግ ደንበኛውና ድርጅቱ እኩል ሥጋቱን የሚጋሩት (የጭሪውን 50 በመቶ) የዋጋ ማስተካከያ ታክሎበት ውል ይፈርማሉ፣ የደረጃው ተገቢ ክፍያም በደንበኛው ይከፈላል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ የኮቪድ-19 ሁኔታ ከለየለት በኋላ ወደፊት በሚተከል ዋጋ ለማስማማት ፈቃደኛ የሆኑ ደንበኞች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ አሁን የወጣውን የውል ዋጋ አምስት ፐርሰንት በራሱ በደንበኛው ሂሳብ አሳግዶ (block in personal account) በማምጣት ከ90 ቀናት በኋላ በሚወጣው የተረጋገጠ፣ ቁርጥ (fixed)  ዋጋ ይስተናገዳል፡፡ ሆኖም በዝግ ሂሳብ ሲያስቀምጥ የነበረው የውል ዋጋ ከዋጋ ማስተካከያው ጋርም ቢሆን ከቁርጥ (fixed) ዋጋው ውል የተሻለ ሆኖ ካገኘው በዚያው ገንዘቡን ባሳገደበት ዋጋ፣ በዋጋ ማስተካካያ ውል መስተናገድ ይችላል፡፡ የሚፈረመው ውል ደንበኛው በዝግ ሂሳብ ካስቀመጠበት ቀን በኋላ የተሠራውን የ90 ቀን የሥራ ሂደት ያገናዘበ ይሆናል፡፡

ለኮሮና ወረርሽኝ የታቀደ ምን አለ

የኮረና ወረርሽን በዚህ ሰዓት መምጣቱ ለሁሉም ፕሮጀክቶች ባጠቃለይ ተጨማሪ ከፍተኛ ስጋት ቢሆንም ፤ ነባር ችግሮችን ለመፍታት በፍሊንትስቶን ከፈጠርነው አቅም አንጻር የሚከተሉት ውጤታማ እንድንሆን አድርገውናል ፡፡ እነዚህም፤

1. ለሰራተኞች ደህንነት ቅድሚያ በመስጠትና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የወረርሽኙን መመሪያን የመፈጸም ዝግጁነታችን መጠናቀቁ

2. የመመሪያውን መሥፈርት አሟልተን በአደይ በሻሌ ላይ ካምፕ ገብቶ ስራውን የሚያንቀሳቅስ ከፍተኛ የሰው ኃይል አቅም መፍጠራችን

3. ለደንበኞች ስጋት በከፊል መወገድ (ከላይ ይመልከቱ) ስትራክቸር ላይ ያደላ ፈጣን እና ጥልቅ ፕሮግራም መዘጋጀቱ (crash program)

በአሁኑ ሰዓት ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከሚገኝ ጠቅላላ ኃይል ወደ 2/3 ኛ የሚጠጋውን በአደይ በሻሌ ፕሮጀክት ላይ አሰማርቷል፡፡ የተሰማራው የሰው ኃይል እና ማሽነሪ እንዲሁም ማቴሪያል ከፕሮጀክቱ ፍላጎት ትንሽ የበለጠ እንዲሆን በመደረጉም መጠነኛ አቅም በሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢ ፕሮጀክቶች ላይ አጋዥ ሆነው ይሰማራሉ፡፡

ወቅቱ ከፍተኛ ሀላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑም የስራ አስፈጻሚ ቦታዎችን ለቀው ዞር ብለው የነበሩት የድርጅቱ አንጋፋ መሐንዲሶች፣ ማለትም መስራቹ ፀደቀ ይሁኔ እና የረጅም ጊዜ አጋርና ሸሪካቸው ታደሰ ጌታቸው ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡  ሁለቱም ለሪል ስቴት ዘርፍ ምክትል ሀላፊው ብሩክ ሽመልስ እና ለኢንጂነሪንግ ግዥና ፋይናንስ ዘርፍ ምክትሉ ሞገስ ታደሰ አጋዥ ሆነው በቀጥታ ስራው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ አቶ መስፍን ታደሰ አሁንም የሥራ አስፈጻሚነት ቦታውን በኃላፊነት እንደያዙ ሲሆን የታደሰና የፀደቀ እገዛ የሥራ አስፈጻሚውንም ኃላፊነት ይሸፍናል፡፡

የኦፐሬሽን ስራው አጣዳፊነት እና ወሳኝነትን በመገንዘብ የሁሉም ሳይቶች ሱፐርቪዥን በዲጂታል ካሜራ አፍታ በአፍታ /real time streaming / እየተካሄደ ሲሆን ደንበኞች ወደሳይት ሳይጓዙ ይህንን ወቅታዊው መረጃ ለማግኘት ከፈለጉ በኮሚቴው በኩል መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ለተጨማሪ ወቅታዊ መረጃ የዜና አምዳችንን ይመልከቱ...

ይህ መረጃም በዋነኛነት ለአደይ በሻሌ ሳይት ደንበኞች የተዘጋጀ ሲሆን በሌሎች ሳይቶች ላይ ወቅታዊ መረጃዎችን በተመሳሳይ መልኩ እናሳውቃለን ፡፡

መረጃውን የሚጠቀም ማንኛውም ሦስተኛ ወገን ድህረ ገጹን ከተገኘበት ዕለት ጋር እንደ ምንጭ  መግለጽ ይኖርበታል፡፡

ማንኛውም እንዲመለስሎት የሚፈልጉት ጥያቄ፤ አስተያየት ፤ ሀሳብ ካልዎት flintstonehomes@gmail.com ላይ መልዕክት ያስቀምጡልን 

Subscribe for updates

Subscribe for updates about Flintstone Homes, get notification for new offers and promotions.

Find us on Social Media